(1) አ.ለ.ረ (አሊፍ ላም ራ፤ ይህ ቁርአን) ሰዎችን በጌታቸው ፈቃድ ከጨለማዎች ወደ ብርሃን አሸናፊ ምስጉን ወደ ኾነው፡፡ ጌታ መንገድ ታወጣ ዘንድ ወዳንተ ያወረድነው መጽሐፍ ነው፡፡
(1) አ.ለ.ረ (አሊፍ ላም ራ፤ ይህ ቁርአን) ሰዎችን በጌታቸው ፈቃድ ከጨለማዎች ወደ ብርሃን አሸናፊ ምስጉን ወደ ኾነው፡፡ ጌታ መንገድ ታወጣ ዘንድ ወዳንተ ያወረድነው መጽሐፍ ነው፡፡
(2) አላህ ያ በሰማያት ያለው በምድርም ያለው ሁሉ የርሱ ብቻ የኾነ ነው፤ ለከሓዲዎችም ከብርቱ ቅጣት ወዮላቸው፡፡
(3) እነዚያ የቅርቢቱን ሕይወት ከመጨረሻይቱ ሕይወት ይበልጥ የሚወዱ ከአላህም መንገድ የሚያግዱ መጥመሟንም የሚፈልጉዋት ናቸው፡፡ እነዚያ በሩቅ ስሕተት ውስጥ ናቸው፡፡
(4) ከመልክተኛ ማንኛውንም ለእነርሱ ያብራራላቸው ዘንድ በወገኖቹ ቋንቋ እንጂ በሌላ አልላክንም፡፡ አላህም የሚሻውን ያጠማል፡፡ የሚሻውንም ያቀናል፡፡ እርሱም አሸናፊው ጥበበኛው ነው፡፡
(5) ሙሳንም ወገኖችህን ከጨለማዎች ወደ ብርሃን አውጣ አላህንም ቀኖች አስገንዝባቸው በማለት በተዓምራታችን በእርግጥ ላክነው፡፡ በዚህ ውስጥ በብዙ ታጋሽና በብዙ አመስጋኝ ለኾኑት ሁሉ በእርግጥ ተዓምራቶች አሉ፡፡
(6) ሙሳም ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ (አስታውስ)፤ ከፈርዖን ቤተሰቦች መጥፎን ቅጣት የሚያቀምሱዋችሁ ወንዶች ልጆቻችሁንም የሚያርዱ ሴቶቻችሁንም የሚተዉ ሲኾኑ በአዳንናችሁ ጊዜ በእናንተ ላይ (የዋለላችሁን) የአላህን ጸጋ አስታውሱ፡፡ በዚህም ከጌታችሁ የኾነ ታላቅ ፈተና አለበት፡፡
(7) ጌታችሁም «ብታመሰግኑ በእርግጥ እጨምርላችኋለሁ ብትክዱም (እቀጣችኋለሁ) ቅጣቴ በእርግጥ ብርቱ ነውና» በማለት ባስታወቀ ጊዜ (አስታውሱ)፡፡
(8) ሙሳም አለ «እናንተም በምድር ያለውም ሁሉ በመላ ብትክዱ አላህ በእርግጥ ተብቃቂ ምስጉን ነው፡፡»
(9) የእነዚያ ከናንተ በፊት የነበሩት የኑሕ ሕዝቦች የዓድም የሰሙድም የእነዚያም ከእነሱ በኋለ የነበሩት ከአላህ በስተቀር ሌላ የማያውቃቸው (ሕዝቦች) ወሬ አልመጣላችሁምን መልክተኞቻቸው በማስረጃዎች መጧቸው፡፡ እጆቻቸውንም (በቁጭት ሊነክሱ) ወደ አፎቻቸው መለሱ፡፡ አሉም «እኛ እናንተ በርሱ በተላካችሁበት ነገር ካድን እኛም ወደርሱ ከምትጠሩን ነገር አወላዋይ በኾነ ጥርጣሬ ውስጥ ነን፡፡»
(10) መልክተኞቻቸው «ከኀጢአቶቻችሁ እንዲምራችሁ ወደ ተወሰነ ጊዜም (ያለ ቅጣት) እንዲያቆያችሁ የሚጠራችሁ ሲኾን ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ በኾነው አላህ (በመኖሩ) ጥርጣሬ አለን» አሏቸው፡፡ (ሕዝቦቹም) «እናንተ ብጤያችን ሰው እንጂ አይደላችሁም አባቶቻችን ይገዙት ከነበሩት ልትከለክሉን ትሻላችሁ፡፡ ግልጽንም አስረጅ (ካመጣችሁት ሌላ) አምጡልን» አሉ፡፡
(11) መልክተኞቻቸው ለእነርሱ አሉ «እኛ ብጤያችሁ ሰው እንጂ ሌላ አይደለንም ግን አላህ ከባሮቹ በሚሻው ሰው ላይ ይለግሳል፡፡ ለእኛም በአላህ ፈቃድ እንጂ ማስረጃን ልናመጣላችሁ አይገባንም፡፡ በአላህም ላይ ምእምናኖች ይጠጉ፡፡
(12) «መንገዳችንንም በእርግጥ የመራን ሲኾን በአላህ ላይ የማንመካ ለእኛ ምን አለን በማሰቃየታችሁም ላይ በእርግጥ እንታገሳለን፡፡ በአላህም ላይ ተመኪዎች ሁሉ ይመኩ፡፡»
(13) እነዚያም የካዱት ለመልክተኞቻቸው «ከምድራችን በእርግጥ እናወጣችኋለን፤ ወይም ወደ ሃይማኖታችን በእርግጥ ትመለሳላችሁ» አሉ፡፡ ወደእነርሱም ጌታቸው እንዲህ ሲል ላከ «ከሓዲዎችን በእርግጥ እናጠፋለን፡፡
(14) «ከእነሱም በኋላ ምድሪቱን በእርግጥ እናስቀምጣችኋለን፡፡ ይኸ በፊቴ መቆሙን ለሚፈራ ዛቻዬንም ለሚፈራ ሰው ነው፡፡»
(15) እርዳታንም (ከአላህ) ፈለጉ፤ (ተረዱም)፡፡ ጨካኝ ሞገደኛ የኾነም ሁሉ አፈረ፡፡
(16) ከስተፊቱ ገሀነም አለበት፡፡ እዥ ከኾነም ውሃ ይጋታል፡፡
(17) ይጎነጨዋል፤ ሊውጠውም አይቀርብም፡፡ ሞትም ከየስፍራው ሁሉ ይመጣበታል፤ እርሱም የሚሞት አይደለም፡፡ ከስተፊቱም ከባድ ቅጣት አለ፡፡
(18) የእነዚያ በጌታቸው የካዱት ሰዎች ምሳሌ (መልካም) ሥራዎቻቸው በነፋሻ ቀን ነፋስ በርሱ እንደ በረታችበት አመድ ነው፡፡ በሠሩት ሥራ በምንም ላይ (ሊጠቀሙ) አይችሉም፡፡ ይህ እርሱ ሩቅ ጥፋት ነው፡፡
(19) አላህ ሰማያትንና ምድርን በእውነት የፈጠረ መኾኑን አታይምን ቢሻ ያጠፋችኋል፡፡ አዲስ ፍጡርንም ያመጣል፡፡
(20) ይህም በአላህ ላይ አስቸጋሪ አይደለም፡፡